የዋጋ ንረት በዋናነት የሚከሰትባቸው መንገዶች
የዋጋ ንረት በዋናነት የሚከሰትባቸው መንገዶች ሁለት ሲሆኑ እነሱም…..
#አንደኛው፡- ፍላጎት የሳበው የዋጋ ንረት (Demand-Pull Inflation)፡- የዚህ አይነቱ የዋጋ ንረት አጠቃላይ ፍላጎት ከአጠቃላይ አቅርቦት ሲበልጥ የሚወለድ ነው። ምክንያቱም እጥረት አለና ሸማች ይሻማል፣ ሻጭ ሽምያው ይመቸውና ዋጋዉን ያንራል! በኢትዮጵያ ከብዙ ነገር አንፃር መሰረታዊ ሸቀጦች ላይ ያለን ፍላጎት ተመሳሳይ በመሆኑ ከአቅርቦቶቻቸው በላይ እንፈልጋቸዋለን። ስለዚህም በየጊዜው ይወደዱብናል። ለአንድ ቁስ ያለን የግል ፍላጎት በገቢ እድገት፣ በሸማች ብዛት፣ በጣዕም ለውጥ፣ አማራጭ ምርት በማጣት ወዘተ ሊያድግ ሲችል፡፡ የህዝብ ቁጥር መጨመር እንዳለ ሆኖ፤ ለአጠቃላይ ፍላጎት እድገት መነሻዎች ከታች ተዘርዝረዋል።
ፍላጎት ለሳበው የዋጋ ንረት መንስኤዎች
1. የብር ዋጋ መውደቅ (Devaluation)
የብር ዋጋ ወደቀ ማለት ዶላር ወይም ሌላ ገንዘብ ተወደደ ማለት ነው። ስለዚህ የገቢ ንግድ ዋጋ ይጨምርብናል። ምናልባት ጥቂት ብቻ እናስመጣለን። ነገር ግን የውጭ ገንዘብ ዋጋ ከፍ ስላለ ለውጭ ዜጎች ምርትና አገልግሎታችን ርካሽ ስለሚሆኑ ብዙ ይገዙልንና የላኪ ገቢያችን ይጨምርልናል። ይህ ደግሞ በአጠቃላይ ጂዲፒያችን ላይ የራሱ የሆነ በረከት ስላለው አጠቃላይ የሀገር ውስጥ ፍላጎት ከሀገር ውስጥ አቅርቦት ይበልጣል። ሰሞኑ የኢትዮጽያ የላኪ ንግድ እንዳደገ ሰምተናል። ሆኖም ለውጭ ምርቶች ያለን ጣዕም ከኢኮኖሚክስ ቲዮሪ የወጣ እንቆንቅልሽ ነው። ይህም በረከሰ ብራችን የተወደደውን ዶላር እየገዛን የውጭ ካልሆነ አንነካም የምንለው ነገር ነው!
2. የጥሬ ገንዘብ በኢኮኖሚ መጥለቅለቅ
ሰው ሁሉ ኪሱ ከሞላ መሸመት መሽሞንሞንና መዝናናት አይጠላም። ምክንያቱም ጥሬ ገንዘብ ወይም ኪስ የመግዛት አቅም ነው። ግን የምንሸምተው ምርትና አገልግሎት እንደ ጥሬ ገንዘብ በቀላሉ ታትሞ የሚደርስ ስላልሆነ ያለውን ስንሻማ ዋጋ እየናረ ይሄዳል ማለት ነው። ከደርግ ወዲህ የኢትዮጽያ ኢኮኖሚ በጥሬ ገንዘብ ጎርፍ ተጥለቅልቆ እንዳለ ተጠንቷል፣ ውጤቱም ዛሬ ከሁላችን ቤት ዘልቋል። በዚህ ወቅት የአብዛኞቻችን ስራ ወደ ባንክ መሰለፍ፣ መመላስ ሆኗል። ስለዚህም አንዳንድ አካባቢዎች ያሉ ባንኮች ብር እንደ ዘይት በኮታ እየሰጡ ይገኛል፣ ብር በብር የሚገዛበት አካባቢ እንዳለ ሰምተናል። ይህ እንግዲህ አንድም ረክሶ የነበረውን ብር ለማስወደድ የሚደረግ ጥረት ሁለትም የዋጋ ንረቱ ግፊት ነው።
3. ዝቅተኛ የወለድ ምጣኔ
ዝቅተኛ ወለድ ትንሽ የመቆጠብ ትልቅ የመበደር ፍላጎትን ይወልዳል። ቁጠባ ማለት ነገ ወለድ ለማግኘት ሲባል ዛሬ የሚታለፍ ፍጆታ ነው። ወለድ እንግዲህ መፍጀት ለሚወዱ መቅጫ ነው። በኛ ሀገር ግን መቶ ብር ተበድረህ አመቱን ሙሉ ሰርተህበት የአንድ ብርጭቆ ሻይ ዋጋ ብቻ የምትቀጣበት ከሆነ መበደር እርካሽ ነው። መቶ ብር ባንክ አስቀምጠህ በዓመቱ ዋጋው ሰባ ሁለት ብር ብቻ ሆኖ የሚጠብቅህ ከሆነ ግን ለምን ትቆጥባለህ? ዛሬዉኑ ብትሸምትበት አይሻልም?፣ በተጨማሪ ሸማች የገቢ ግብር ሲቀነስለት እና ገቢው ሲጨምር እንዲሁም በመጪው ጊዜ ላይ ያለው መተማመን እየጨመረ ሲመጣ ከፍተኛ የመሸመት ፍላጎት ሊያሳይ ይችላል፡፡
4. የውጭ ንግድ አጋሮቻችን እድገት
አለም ዓቀፍ የንግድ አጋሮቻችን ፈጣን እድገት ካስመዘገቡ ከኛ የሚሸሚቱት ሸመታ ይጨምራል። የውጭ ምንዛሬ ግኝት ከፍ ይላል። ፍላጎታችንም አብሮ ያድጋል። ታዲያ ዋጋ መች ቆሞ ይጠብቃል፣ ይሮጣል!
#ሁለተኛው፡- ወጪ የገፋው የዋጋ ንረት (Cost-Push Inflation)፡- ወጪ የግብዓቶች ዋጋ ነው። የግብዓት ዋጋ (የሰራተኛ፣ የጥሬ እቃ፣ የነዳጅ፣ የሀይል፣ የካፒታል ወዘተ) ዋጋ ጨመረ ማለት የምርቱ/የአገልግሎቱ ዋጋም ይጨምራል ማለት ነው። ማንኛውም አምራች ለትርፍ እንጅ ለፅድቅ ስለማይሰራ የቤት ኪራይ፣ የመኪና ኪራይ፣ የመሬት ኪራይ፣ የሰራተኛ ደሞዝ፣ የብድር ወለድ ወዘተ እና የራሱን ትርፍ ሳያሰላ ለምርቱ ዋጋ አይተምንም። በአጭሩ ወጪ ሲጨምር ዋጋ ይጨምራል። ወጪ በቋምነት ሲያድግ ደግሞ ዋጋ ይንራል።
የወጪ የገፋው የዋጋ ንረት መንስኤዎች
1. የስብጥሩ ወጪ ማደግ
የግብዓት ወጪና የሌሎች የምርት ስብጥሮች ዋጋ መናር የምርቱን የአገልግሎቱን ዋጋ ያንረዋል። ነዳጅ ሲወደድ ሁሉም ነገር ይወደዳል፤ ስንዴ ሲወደድ ዳቦ ይወደዳል! የሰራተኛ የጉልበት ዋጋ ሲወደድ ምርትና አገልግሎት ይወደዳል!
2. ተተንባይ የዋጋ ንረት
ሰዎች የዋጋ ንረቱ አይቀሬ ነው ብለው ካሰቡ በእጃቸው ያለውን ሀብት አስወድደው ስለሚሸጡ ለአምራቹ ወጪው ይጨምራል። እርሱም አምርቶ ሲጨርስ አስወድዶ ይሸጣል!
3. ከፍተኛ ኢ-ቀጥተኛ ግብር ሲኖር
አምራች ከፍተኛ ተዘዋዋሪ ግብር ሲጫንበት በምርቱ ዋጋ ላይ በማካተት ወደ ሸማቹ ያዞራል። ስለዚህ ሸማች ግብር ሶስቴ ይከፍላል-በመጀመሪያ ከገቢው፣ ቀጥሎ በተዘዋዋሪ የሻጭን ድርሻ ሶስተኛ ቫት !ቫት ምንድን ነው ቢሉት "ክትፎ በልተህ ለመንግስት ዱለት መጋበዝ ነው!" አለ እንደተባለው!
4. የውጭ ምንዛሬ መወደድ ወይም የብር ምንዛሬ መርከስ
እውነቱን ለመናገር ብራች የመግዛት አቅሙ ተዳክሟል። አንድ ኩንታል ቡና ልከን አንዲት ስማርት ፎን ማስመጣት መቻላችንን እንጃ! በዛ ላይ ቀረጡ፤ ትራንስፖርቱ፤ የማከፋፈያው እና የመሸቀጫ ዋጋዎች ሲጨመርባቸው ወጪው የት ነው?
5. የሞኖፖሊስቶች መኖር
ብቸኛ አምራች ብቸኛ ሻጭ በዋጋ ላይ ፈላጭ ቆራጭ ነው። ምክንያቱም በወጪው ላይ ያን ያህል ጠንቃቃ አይደለም፣ ምርቱ ተተኪ የለውም፣ የህግ ወይም የእውቀት ከለላ አለው። በሙሉ አቅሙ አያመርትም። እናም ሞኖፖሊስቱ ከፈለገ ከአቅም በታች በማምረት ምርቱ አሳንሶ ዋጋውን ማናር ይችላል። በሀገራችን ያሉት ጥቂት አምራች እና አስመጪ በመሆናቸው እንዲሁም ትላልቅ የመንግስት ሞኖፖሊ ኩባንያዎች በቢልዮኖች አተረፍን የሚሉት በእንደዚህ አይነቱ ፈላጭ ቆራጭነት አሰራር ነው።
ሃሳቡን እንዳጋራችሁ የላከልኝ Kidane Alemu Ago ነው!
ሃሳቡ በግራፍ ሲገለጽ
#ለምሳሌ፡- ከታች በግራ በኩል ያለው ግራፍ (Cost Push) እንደሚያሳየው በተጠቀሱ ምክንያቶች የማምረቻ ወጪ ሲጨምር ጠቅላላ የአቅርቦት መጠን ከSRAS1 ወደ SRAS2 መቀነሱን ተከትሎ ፍላጎት ካለበት ብዙም ስለማይንቀሳቀስ ዋጋ ከP1 ወደ P2 ይጨምራል፡፡
#ለምሳሌ፡- ከታች በቀኝ በኩል ያለው ግራፍ (Demand Pull) እንደሚያሳየው ከላይ በተጠቀሱ ምክንያቶች ጠቅላላ ፍላጎት ከAD1 ወደ AD2 ማደጉን ተከትሎ አቅርቦት ካለበት ብዙም ስለማይንቀሳቀስ ዋጋ ከP1 ወደ P2 ይጨምራል፡፡
Post a Comment
0 Comments