#የጣሳ_ግብርና!


ድሮ ድሮ የጓሮ አትክልቶች መትከል እና መንከባከብ እንደ መዝናኛ ተግባር ነበር የሚቆጠረው! አሁን ላይ የጓሮ አትክልቶች መትከል እና በአግባቡ መንከባከብ የምግብ ዋስትና ከሚጠበቅባቸው መንገዶች አንዱ ሆኗል (በተለይ በዚህ ወቅት የከተማ ግብርና የፖሊሲ ማዕቀፍ የሚፈልግ ነው)፡፡


በቀላሉ የጓሮ አትክልት ቦታዎች በመኖሪያ አካባቢ አቅራቢያ በመሆናቸው እና ትንንሽ ስፋት የሚፈልጉ ከመሆናቸው በተጨማሪ በሰፋፊ ማሳዎች ተመርተው ረጅም እርቀት ተጓጉዘው በገበያ ከሚገኙ ምግቦች በወጪም በፍሬሽነትም ተመራጭ ያደርጋቸዋል፡፡ 


በአብዛኛው ከተሞች በመሰረታዊ ቁሶች የገጠሩ ጥገኞች ናቸው! በተለይ በኢትዮጵያ ገጠር ማለት የከተሞች ሳምባ ማለት ነው፡፡ ከተሞች ዋና የኑሮ ግብዓቶችን ከገጠሩ ክፍለ ኢኮኖሚ ይወስዱ እና ለገጠሩ ክፍለ ኢኮኖሚ እድገት የሚያዋጡት ከሚጠበቀው አንጻር ዝቅተኛ ነው፡፡


የምግብ ቁሳቁስ የሚያመርተው ገጠሩ ነው! #ለምሳሌ፡- ስንዴ በገጠሬው ሲመረት የከተሜው ሃላፊነት ዱቄት፤ ዳቦ፤ ብስኩት እና ኬክ አድርጎ መመገብ ነው፤ ገብስን ገጠሬው ሲያመርት ከተሜው ቢራ ጠምቆ መጠጣት ነው፤ ገጠሬው የቅባት እህል ሲያመርት ወደ ምግብ ዘይትነት መቀየር የከተሜው ድርሻ ነው፤ ገጠሬው ዛፎች ሲያለማ እንጨት ለከተሜ ግንባታ ግብዓት ነው፤ ገጠሩ አትክልቶችን ሲያመርት ለከተሜው ኩሽና መሰረት ነው፤ ገጠሩ ከብቶችን ሲያረባ ለከተሜው ጫማ ዋስትና ነው፤ ወዘተ፡፡


ለገጠሬው ገንዘብ ከፍለነው ነው የገዛነው የሚል ሰው ካለ ገንዘብ ለአርሶ አደሩ #የምርታማነት ደረጃውን ለማሻሻል ካልጠቀመው ምንም ዋጋ የለውም! ትንሽ ቆይቶ አርሶ አደሩ በከተማ እራሱም ሸማች ሆኖ መቅረቡ አይቀርም፡፡ ስንዴ የሚያመርት አርሶ አደር የስንዴው ማሳ ምርት እና ምርታማነት እንዲሻሻል የሚፈልጋቸው ዘመናዊ ግብዓቶች ከጊዜው ጋር ካልተሟሉለት፡ ምርታማነት እየቀነሰ ነው የሚሄደው፡ ስለዚህ ከተማው ገጠሩን መደገፍ ያለበት ለራሱም ሲል ነው፡፡ 


ገጠሬው ሲፈተን እና ሲጎልበት ከተሜው ኢኮኖሚያዊ ጫናው በዋጋ ንረት በኩል በቀጥታ ይደርሰዋል! ነገር ግን በከተማ ያሉ ተቋማት እና ማህበረሰብ የገጠሬውን ሸክም በተወሰነ መልኩ ማቃለል የሚችሉባቸው መንገዶች አሉ፡፡ #ለምሳሌ፡- ምርጥ ዘር በምርምር በመፍጠር፤ ጸረ ሰብል ማጥፊያ ኬሚካሎችን በመፍጠር፤ አዳዲስ አሰራር ስልቶችን በመፍጠር፤ የግብርና መሳሪያዎችን በመፍጠር፤ ፍታዊ ዋጋ በማቅረብ፤ በገጠሩ የተመረቱ ምርቶችን እሴት በመጨመር፤ በጠባብ ቦታዎች የሚመረቱ ምርቶችን በማምረት በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ እራሳቸውን መደገፍ አለባቸው፡፡


በገጠር የማሳ ጥበት፤ የግብዓት እጥረት/ውድነት፤ የውሃ እጥረት/የዝናብ ጥገኝነት፤ ደካማ የመሬት አስተዳደር (የመንግስት ቢሮክራሲ) እና የቤተሰብ ብዛት ምርት እና ምርታማነትን በሂደት ይቀንሱታል! ከተማው በመኖሪያ አካባቢው ከፍተኛ የውሃ እና የቦታ አቅርቦት ሳያስፈልገው በፍላጎት ብቻ ቤተሰባዊ ፍጆታውን መደጎም ይችላል፡፡


ብዙ ሀገራቶች የከተማ ግብርና ማበረታቻ (Urban Farm Initiative) ስልቶችን ይተገብራሉ! በኢትዮጲያም በተመሳሳይ ሙከራ አለ ነገር ግን ከምንጊዜውም በላይ የከተማ ግብርና ስራዎች የሚያስፈልጉበት ወቅት አሁን መሆኑን እረዳለሁ፡፡


#ለምሳሌ፡- አዲስ አበባ ብዙ ህዝብ፤ ከተፈተሸ ሰፊ ቦታ (ወደ ላይ ጭምር (Vertical Farming))፤ ከፍተኛ ስራ አጥነት እና የኑሮ ውድነት ያለባት ከተማ ነች፡፡ ይህ ብቻውን የከተማ ኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎችን ከግብርና አንጻር በተለየ አቅጣጫ መመልከት ለመጀመር በቂ ነው፡፡


የከተማ ግብርና በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ላላቸው፤ ስራ አጥ ለሆኑ እና ለሴቶች ሊኖረው የሚችለው ፋይዳ ግልጽ ነው፡፡ የዓለም የምግብ ድርጅት (FAO) በአለም ላይ ከ200 ሚሊየን ህዝብ በላይ ዋነኛ ገቢውን በብቸኝነት ከከተማ ግብርና ያገኛል (12% የሚሆነውን የዓለም ህዝብ ይመግባሉ) ሲል ይገምታል፡፡


በተባበሩት መንግስታት ሪፖርት በሻንጋይ ግዛት ውስጥ የሚገኙ ትንንሽ ከተሞች በከተማ ግብርና ከ30-85% የሚሆነውን አትክልቶች ለፍጆታነት ለገበያ ያቀርባሉ፤ በኬንያ 17% የሚሆነው ከብቶች የሚረቡት በከተማ ነው፤ በደቡብ አሜሪካ ቤተሰቦች በሳምንት አንድ ቀን ብቻ በጓሮ አትክልት ስፍራቸው ሰርተው የምግብ ወጪያቸውን ከ10-30% ይቀንሳሉ ሲል አውጥቷል፡፡ በተመሳሳይ በአንድ ጥናት በአለም ላይ በ2020 ብቻ በከተማ ግብርና ከ213 ቢሊየን ዶላር በላይ ተንቀሳቅሷል ተብሎ ይገመታል፡፡


የከተማ ግብርና በቤት ውስጥ፤ በጓሮ፤ በህንጻ ጣሪያ ላይ፤ ታጥረው በተቀመጡ ክፍት ቦታዎች ላይ፤ ወዘተ በመጠቀም አትክልት (ጎመን፤ ሽንኩርት፤ ቃሪያ፤ ቲማቲም፤ ጥቅል ጎመን፤ ሰላጣ፤ ሮዝመሪ፤ ወዘተ)፤ እንጉዳይ፤ ቦለቄ (በተለይ የጊቢ አጥሮች ላይ)፤ ዶሮ፤ ከብቶች (አርብቶ መሸጥ ወይም ለወተት ምርት)፤ የተወሰኑ ቋሚ ፍራፍሬዎች፤ ሌላው ቀርቶ በጓሮ የሚኖር ጤና አዳም እና ዳማከሴ ያለው ጥቅም ማንም የሚያውቀው ነው፡፡


ለከተማ ግብርና በቤተሰብ ደረጃ የቦታ እጥረት የሚል ምክንያት በተደጋጋሚ ይነሳል (በጊቢ ውስጥ 50 ካሬ የሚሆን መሬትን በሳር የሸፈነ ቤተሰብ ለምግብ ዋስትናው ማሰብ አለበት) ነገር ግን ባለ አነስተኛ ቦታ አጠቃቀሙን በማሻሻል መስራት ይቻላል (ቤተሰቡ በሳምንት አንድ ቀን ለምሳ የሚሆን ግብዓት ከጓሮው ከሰበሰበ የሚናቅ አይደለም)።


ከተሞችን የሚያስተዳድሩ አካላት የታጠሩ ሰፋፊ ቦታዎች ወደ ስራ እስኪገቡ በጊዚያዊነት ለምርት ቢውሉ ምንም ጉዳት አያመጡም፤ በክርክር፤ በእዳ ምክንያት፤ በግብዓት እጥረት የቆሙ የመንግስት እና የግለሰብ ህንጻዎች ብዛት በሺዎች ነው፡፡ ስለዚህ አሰራሮችን በማውጣት በጊዚያዊነት ለከተማ ግብርና ቢውሉ ጉዳቱ ምንድን ነው?


የግለሰቦት እና የመንግስት ህንጻዎች ተሰርተው ሲጠናቀቁ በጣሪያቸው በተጠና መልኩ የተወሰነ አትክልቶችን እንዲይዙ ቢደረግ ጉዳቱ ምንድን ነው? (የዓለም ተሞክሮ ነው!) አሁን ላይ አትክልት መትከል አፈር ደልድሎ መዝራት ማለት አይደለም! በውስን እቃዎች ላይ ፍሳሽ አወጋገድን ተከላክሎ መትከት/ማብቀል ይቻላል፡፡


ምንም ስለ ግብርና የማያውቅን ከተሜ በቀላሉ አትክልት ትከል፤ ዶሮ አርባ፤ ከብት አደልብ በማለት ብቻ ለውጥ አይመጣም፡፡ ተቋማት ስልጠና፤ የዘር አቅርቦት፤ አነስተኛ ብድር አቅርቦት፤ ማህበራትን ማሳመን/ማደራጀት፤ ግብዓት አቅርቦት፤ ገበያ ማመቻቸት፤ የውሃ/በተለይ የከርሰ ምድር ውሃ አቅርቦት፤ ወዘተ ማድረግ ይገባል (በቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከዘፈን ሰዓት ቀንሶ የከተማ ግብርና አሰራሮች፤ ጥቅሞች እና ተሞክሮዎችን በተደጋጋሚ በማቅረብ ሰዎችን ማነሳሳት ይቻላል)፡፡



ማህበረሰቡ ለራሱ ሲል! መንግስትም ለራሱ ሲል! የከተማ ግብርናን እግረ መንገድ ሳይሆን በልዩ ትኩረት መቀላቀል እና ጥቅሙን ማወቅ አለበት፡፡ አዲስ አበባ በተበጣጠሰ መልኩም ቢሆን ማለትም ግለሰቦች በጊቢያቸው፤ ትምህርት ቤቶች በጓሮቿቸው፤ በመንግስት/በግል ተቋማት ቅጥር ጊቢ፤ ወዘተ በትጋት 10 ሄክታር የሚሆን ሽንኩርት ተተክሎ ቢሆን ብላችሁ አስቡት!