#ወጪ_መቀነሻ_ስልቶች!

የዋጋ ንረት እና የገቢ ማነስ የፈጠሩትን የኑሮ ውድነት ለመቋቋም በግለሰብ እና በቤተሰብ ደረጃ የሚሰሩ ስራዎች ሚናቸው ከፍተኛ ነው፡፡ አስቸጋሪ ወቅቶች የመንግስትም የግለሰቦችም የጋራ ትብብር የሚፈልጉ መሆናቸው ይታወቃል!፡፡


የኑሮ ውድነትን ለመታገል ወጪ ቆጣቢ አኗኗርን መለማመድ እንዲሁም የበጀት አጠቃቀምን መከለስ በጣም አስፈላጊ ነው! የበጀት አጠቃቀም ቋሚ ሊሆን አይችልም! ተለዋዋጭ ነው! (#ለምሳሌ፡- ቤተሰቡ ጋር የሚኖር ብቻውን መኖር ሲጀምር፤ ያላገባ ሲያገባ፤ ያገባ ሲወልድ፤ የልጆች ቁጥር ሲጨምር፤ የቤት ሰራተኛ ሲቀጥር፤ ትምህርት ሲጀምር፤ በዓል ሲደርስ፤ ትራንስፖርት፤ መብራት፤ ውሃ ሲቆራረጥ፤ ስልኩን 4ጂ ሲያደርግ፤ ቤት ሲቀይር፤ ህመም ሲከሰት፤ ወዘተ)፡፡



የዜጎች የኑሮ ሁኔታ እንዲሻሻል የማድረግ ዋነኛ ሃላፊነት የመንግስት ቢሆንም ከሁኔታው ከባድነት ለመላቀቅ ዜጎች የራሳቸውን የበጀት አጠቃቀም በማሻሻል ሁኔታውን ማለፍ ይችላሉ! በሁኔታዎች ከማማረር አቅም የፈቀደው እና የሚቻል በእጅ ውስጥ ያለ አማራጮችን መመልከት ብልሃት ነው፡፡ ለምሳሌ………



1. ወጪን በተመዘገበ ስልት መቆጣጠር፡- ድንገታዊ በሆነ መልኩ ወጪ ማውጣት ሳይሆን መሰረታዊ የሚባሉ የወጪ ዝርዝሮችን በመመዝገብ ለምን? ምን ያህል? እንደሚያወጡ እና እንዳወጡ ማወቅ ሊያደርጉ ለሚያስቡት የኑሮ ማሻሻያ መነሻ መረጃ መሆን ይችላል፡፡ ሁልጊዜ ወጪን ለመቀነስ የሚረዳ እና ከገቢያችሁ ጋር መናበብ የሚችል የበጀት ዝርዝር ማዘጋጀታችሁን ማረጋገጥ፡፡



2. ሸመታን በፕሮግራም እና በዝርዝር ማከናወን፡- ሰዎች ገበያ ከወጡ በኋላ ሳይሆን ከመውጣታቸው በፊት ስለሚሸምቱት ነገር እና መጠን መወሰን፤ ካሰቡት የሸመታ ፍላጎት በላይ በጀት ይዞ ወደ ገበያ ያለመውጣት በጣም ተገቢ ነው፡፡ 



በኢኮኖሚክስ አስተምሮት ውስጥ የሚታወቀውን Budget Line የሚባለውን ሃሳብ በምሳሌ ብናየው፡ ሸማቾች የምስር ዋጋ ጨምሮ ሲጠብቃቸው የማተካካት ስራ መስራት አለባቸው! ምስር ሊገዙ ወጥተው ካሰቡት በላይ ዋጋ ቢንር የጨመረውን ዋጋ ከመክፈል ይልቅ ወይ የምስሩን መጠን ዝቅ አርጎ መሸመት አልያም ምስርን በሌላ የምግብ አማራጭ ተክቶ መመለስ ነው የሚለው (በሀገራችን አብዛኛው ቁሳቁስ ዋጋው የጨመረ መሆኑ ቢታወቅም ትንንሽ የዋጋ ቅናሾችን አለመናቅ ተገቢ ነው)፡፡ 



በፕሮግራም የማይሸምት ሸማች ገበያ ውስጥ ውሳኔ መስጠት ይቸገራል! የሚያምር ልብስ ሲመለከት፤ ታላቅ ቅናሽ የሚል ማስታወቂያ ባየ ቁጥር፤ ሰው ከቦ የሚገዛው እቃ ባየ ቁጥር ሲሸምት ከበጀት ዝርዝሩ መውጣቱ አይቀርም፡፡



#ለምሳሌ፡- ልጆችን ገበያ እግረ መንገድ ይዞ የወጣ ሸማች! ፈተና ውስጥ ነው!፡፡ የጠየቁትን ከፕሮግራም ውጪ ለመግዛት ሊገደድ ይችላል! ቀላሉ ነገር ልጆች የፈለጉትን በሙሉ ለመግዛት ከመሞከር ይልቅ ልጆች ወላጆች ከገቢያቸው አንጻር ለሸመታ ፕሮግራም እንዳላቸው ማስተማር ነው፡፡ ባይ ነኝ!



3. እራስን ከብድር ማላቀቅ፡- ብድር የወጪ ሁኔታን የማዛነፍ አቅም አለው፡፡ ስለዚህ ወደፊት የሚኖር የወጪ ምክንያት እንዳይጨምር ከብድር ራስን ማራቅ! የነበረ ብድር ካለ በፍጥነት በተቻለ አቅም ከፍሎ ከእዳ መላቀቅ፡፡



4. የመኖሪያ አካባቢን መለወጥ፡- ከገቢ አንጻር ሰዎች ተከራይተው የሚኖሩባቸው ቦታዎች/ሰፈሮች ውድ ከሆኑ እና የሚገጥማቸው Opportunity Cost ዝቅተኛ ከሆነ ወደ ተመጣጣኝ ወጪ የሚጠይቁ አካባቢዎች ለውጦ መኖር መጀመር ወጪን ማመጣጠን ላይ ሚናው ቀላል አይደለም፡፡ ዝቅተኛ ገቢ ያለው ሰው ጊዜን ከወጪ እኩል መመልከት አለበት ብዬ አላስብም! አማካይ የጊዜ ብክነት የተሻለ ወጪን ለመቀነስ ወይም የተሻለ ገቢ ለማስገኘት ካስቻለ የሚመረጥ ነው፡፡



#ለምሳሌ፡- ጊዜውን በካፌ ወሬ የሚያጠፋ አንድ ሰው "ባስ ቆሜ ከምጠብቅ በታክሲ ቶሎ ልሂድ" ብሎ ተጨማሪ ወጪ ቢያወጣ በቂ እና አሳማኝ ምክንያት አለው ማለት አይደለም፡፡ 



5. የገበያ ቦታን መወሰን፡- የተሻለ ዋጋ ያላቸው ገበያዎችን መርጦ መሸመት፤ የገበያ ዋጋ ጥናት ቀድሞ ማድረግ፤ ትንንሽ መጠን በየጊዚው ከመሸመት ረዘም ላላ ጊዜ (ቢያንስ ለወር) ቤተሰቡን የሚመግብ አስቤዛ ማድረግ (የተለዋዋጭ ዋጋ ጫናን ይቀንሳል)፤ በጋራ መሸመት የሚቻልበት ሁኔታ ካለ መመልከት፤ ወዘተ፡፡



6. ትንንሽ ወጪዎችን ማስቀረት:- #ለምሳሌ፡- በቤት ውስጥ ማብሰልን መለማመድ (ውጪ መመገብን መቀነስ)፤ ሰራተኞች ከሆኑ ምሳ ሰሀን ይዘው መገኘት፤ የእረፍት ሰዓት የወጪ ልምዶችን መቀነስ (ቡና ሻይ፤ ወዘተ)፤ ርካሽ የትራንስፖርት አማራጭን መጠቀም (አጫጭር እርቀቶችን በእግር መሞከር!)፤ ጫማ በቤት ውስጥ ማጽዳት (ዛሬ ላይ ጫማ ማስቀባት ርካሽ አይደለም!)፤ የጸጉር ወጪን መመዘን፤ የሞባይል ካርድ ወጪን ምክንያታዊ ማድረግ፤ የሃይል ወጪን ፍታዊነት መለካት (ኤሌክትሪክ (ሃይል የሚቆጥብ ስቶቭ መጠቀም ሊሆን ይችላል!)፤ ወዘተ ላይ ትኩረት ማድረግ የሚናቅ ለውጥ አይደለም፡፡



#ለምሳሌ፡- የመንግስት ተቋማት ባላቸው ተቋም ውስጥ ነጻ አንድ ክፍል እና ቁሳቁስ (ወንበር፤ ጠረቤዛ፤ ብርጭቆ፤ ወዘተ)፤ ውሃ እና መብራት በማቅረብ ካፌዎችን በጨረታ አስገብተው አገልግሎት እንዲያቀርቡ እና ለሰራተኞቻቸው በተመጣጣኝ ዋጋ ምሳ እንዲቀርብ ድርድር ቢያደርጉ መጥፎ አይደለም!



#ለምሳሌ፦ የመንግስትም ሆኑ የግል ተቋማት አትክልት ተንከባካቢ ባለሙያ በመቅጠር ባሏቸው ክፍት ቦታዎች፤ አጥር እና የህንፃ ጣሪያዎችን በመጠቀም የጓሮ አትክልት ቢያለሙ ለሰራተኞቻቸው ማበርከት የሚችሉት ምርት አያጡም።